Sunday 5 May 2013

የዳያስፓራ ኢትዮጵያዊነት

ይህ ፅሁፍ በፌስቡክ ላይ በ ItIs Mee -Sunday, 11 November 2012 የተፃፈ ነው

በአሜሪካም ሆነ በምዕራቡ አለም በርካታ ኢትዮጵያዉያን በትምህርትም ሆነ በስደት እንደሚኖሩ ይታወቃል:: ይህ በኢትዮጵያዉያን ብቻ የተወሰነ አይደለም:: በርካታ ሌሎች አፍሪካዉያንም በተመሳሳይ ምክንያቶች ይኖራሉ:: ይህንን የዉዴታም ሆነ የግዴታ ስደት ብናሰላዉ ከ50 አመት በላይ የሆነው እውነታ ነው:: በባርነት ሲያግዙን የነበረውም ቢለካ ከ200 አመታት በላይ ይሆነዋል:: ታዲያ እኛ አፍሪካዉያን በነዚህ በነጮች አለም ስንኖር ለመሃላ ያህል እንኩዋን በሳይንስና ምርምር ለአንዴ እንኳ ከፍተኛ ሽልማቶችን ልናገኝ አልቻልንም:: ለዚህ ደግሞ እኛ አፍሪካዉያን ለሽልማቱ አንሰን ሳይሆን በኛው በራሳችን ምክንያት ወይም በነጮቹ አመለካከት የተነሳ በሚደረግ አድሎዋዊ አሰራር ነው:: ለታላላቅ ቴክኖሎጂዎች የሚጠቀሙባቸውን ጥሬ እቃዎች ከአፍሪካ እያመጡ በዛም አነሰም በኛው በአፍሪካዉያን ትብብርና ጥረት ሰርተው እነሱ ባላቴክኖሎጂ እኛ ደግሞ የድንቁርና ምሳሌ ሆነን እየኖርን ነው:: እርግጥ ነው በአህጉራችን ድንቁርና አለ:: ሆኖም ግን በቀዳዳ አፈትልከው የወጡት ግን የላቀ እውቀት እንዳላቸው በርካታ ማስረጃዎችን ማሳየት ይቻላል:: ምሳሌዎቹን ለGoogle ልተዋቸው:: አሜሪካ ያሉ አፍሪካዉያን ሲታዩ የሚሰሩት ውጤታማ ስራ የራፕ ዘፈን ብቻ ነው ማለት እንችላለን:: ከዛ ባለፈ ያለው የአፍሪካዉያን ስራ ምናልባት ጽዳት ወይም ፓርኪንግ ቢሆን ነው:: እዉን እኛ አፍሪካዉያን ለሌሎቹ የስራ ቦታዎች (በተለይ ለታላላቅ የምርምር ቦታዎች) አንመጥንም? የአፍሪካዉያኑን በዚህ ልግታዉና ወደ ሃበሻ ላጥብበው::
            ከሃገራችን ሰዎች አንዳንድ ወጣ ወጣ ማለት የጀመሩ ነገር ግን በተለያዩ ምክንያቶች ተመልሰው የተቀበሩ ወይም እስከወዲያኛው እንዲሰናበቱ የተደረጉ ምሳሌዎች አሉን:: በአብዛኛው ሃበሻ አመለካከትም ነጮች እኛን በበታችነት እንደሚፈርጁን እና እንደሚጫኑን እናስባለን:: ይህ እውነትም ሃሰትም ሊሆን ይችላል:: መከራከሪያም ማቅረብ አልፈልግም:: ነገር ግን ነጮቹ የዚያችን የሃበሻ ሃገር ማደግ እንደማይፈልጉ የምናስብ ነገር ግን የነሱ ሃገር ተስማምቶን የምንኖር ስንቶቻችን ነን? ሃገራችን ስትነካ ምን ያህል እንቆጣለን? እድሜ ለፌስቡክ የበርካታ ሰዎችን አመለካከት መረዳት ችያለሁ:: እናም በትዝብቴ ያየሁት ፈረንጅ ሃገር የሚኖሩ ኢትዮጵያዉያን ለሀገራቸው ተቆርቋሪ መስለው ይታያሉ:: እኔ ግን በዚህ ተቆርቋሪነት ላይ የራሴን አመለካከት ማንሳት ፈለኩ:: በጥያቄ ልጀምር:: እውን ፈረንጅ ሃገር የሚኖሩ ሃበሾች ሃገራቸውን ይወዳሉ? እውነትስ ከልባቸው ኢትዮጵያዊ ናቸው?
              የግሌ መልስ "ምናልባት 20% የሚሆኑት ይወዱ ይሆናል" ባይ ነኝ:: ሃገርን የመውደድ ልኬቱ በኔና በነሱ ሊለያይ ይችላል:: ለኔ ሃገርን መውደድ ማለት የግል ፍላጎትን እና ምቾትን ለሃገር አሳልፎ መስጠት ነው:: ሃገርን መውደድ ማለት እራስን አሳልፎ እስከመስጠት ማለት ነው:: ሃገርን መውደድ ማለት መከራን እና ችግርን መሸሽ አይደለም:: አንድ ሰው ፓለቲከኛ ሲሆን ለግል ጥቅሙ ሳይሆን ለህዝብና ለሃገር ሊሰራ ቆርጦ ተነሳ ማለት ነው:: ሆኖም ግን አንድ ችግር ሲያጋጥመው የሚኮበልል ከሆነ ቀድሞውኑ የተነሳው ለራሱ ግላዊ ጥቅም እንጂ ለሃገርና ለህዝብ አልነበረም ማለት ነው:: ከዚህ የፓለቲከኞች ቁማር ጋር በተያያዘ የበርካቶችን ታሪክ ማንሳት ይቻላል:: ነገር ግን በተጠየቅ ብቻ ልለፋቸው:- አቶ መለስ ብዙ ግዜ የሚያስበረግጋቸው የዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ስም እንጂ የነ ሃይሉ ሻውል ወይም ግዛቸው ሽፈራው አልነበረም:: አቶ መለስ ማን ለምን አላማ ፓለቲከኛ እንደሆነ ያዉቁ ነበር:: ሆኖም ግን መጨረሻ ላይ የታዘብነውን ታዘብን:: እነዚህን ፓለቲከኞች ስናያቸው ከሞላ ጎደል ሀገራቸውውን ይወዳሉ ወይስ አይወዱም ለሚለው ጥያቄ መልስ እራሳችን መስጠት እንችላለን:: በኔ እይታ ማናቸውም ሃገራቸውን አይወዱም:: ቢወዱ ኖሮ ሞትን ይጋፈጡ ነበር:: በኔ አመለካከት ፓለቲከኛ ለያዘው አላማ ሞትን የሚጋፈጥ እንጂ የሚሞዳሞድ ወይም ወደ ባእድ ሃገር የሚፈረጥጥ አይደለም:: ከጋዜጠኞቻችንም እስክንድር ነጋንና ፈርጣጭ ጋዜጠኞችን ማነጻጸር ይቻላል:: ማን በትክክል ሃገሩን ይወዳል ብለንም እንመዝን:: እኛስ?
          በተለያዩ ሃግሮች ላይ ሃበሾች ሰልፍ ሲወጡ ይታያሉ:: ለምንድን ነው ሰልፍ የሚወጡት? ሀገራቸውን ስለሚወዱ ወይስ በሌላ ምክንያት? ከላይ እንዳልኩት 80%ቱ ምክንያታቸው ሌላ ነው:: ሃገሩንና ህዝቡን የሚወድ ሰው በሩቁ ሆኖ "ሊመታችሁ ነው ተጠንቀቁ" "ሊገላችሁ ነው ሽሹ" ወይም "ገደላቸው ገረፋቸው" እያሉ በባዶ ሜዳ መፈክር ማሰማት አይደለም:: ሃግሩን የሚወድ ሞትንም ቢሆን ተጋፍጦ ለሃገሩ ለውጥ ያመጣል እንጅ በተንዳላቀቀ ኑሮ ላይ ሆኖ እንዲህ እኔ እንደምጽፈው መፈክር እያዘጋጁ መሰለፍ አይደለም:: ከተሰላፊዎቹ መካከል በርካታ የሃገሪቱ አንጡራ ሃብት ፈሶባቸው በከፍተኛ ደረጃ የተማሩ ነገር ግን ብር ስላነሳቸው ብቻ በባእድ ሃገር ከሙያቸው ጋር ፍጹም ግንኙነት የሌለው ስራ እየሰሩ የሚኖሩ ነገር ግን ለሃገር ተቆርቋሪ የሚመስሉ አሉ:: በበርካታ ሺህ የሚቆጠሩ የህክምና ባለሞያዎች ሃገር ቤት ያለ ወገናቸው በበሽታ እያለቀ እነርሱ ግን ብር ፍለጋ ብቻ አሜሪካ ወይም አውሮፓ ገብተው የሾፒንግ ካሸር ወይም የጽዳት ሰራተኛ ሆነው የሚሰሩ አሉ:: እውን እነዚህ ሰዎች ሃገራቸውንና ህዝባቸውን ይወዳሉ? በምርምር ስራቸውና የማስተማር ስራቸው አንቱ ተብለው ሲኖሩ የነበሩ ምሁራን ወደ ፈረንጅ ሃገር መጥተው ከሙያቸው ጋር የማይገናኝ ስራ እየሰሩ ነገር ግን ሰልፍ የሚወጡ እውን ሃገራቸውን ወደው ነው? ሃገርን መውደድ ማለት የደሃ ገንዘቧን አውጥታ ያስተማረችኝን ሃገር ቢያንስ በሙያዬ ሳገለግላት እንጅ ሰባራ ሳንቲም ባላወጣብኝ ሃገር ላይ ሳገለግል አይደለም:: ሃገርን መውደድ ማለት ወገንን ከድንቁርናና ከበሽታ መታደግ ማለት ነው:: ሃገርን መውደድ ማለት ወገንን እና ሃገርን ከጥፋት መታደግ እንጂ መታሰርን ወይም መሞትን መሸሽ አይደለም:: የዛሬ የኛ በገንዘብ ተቸግሮ ሃገሪቱን ማገልገል ማለት የነገውን ትውልድ እንዳይቸገር ማድረግ ነው:: የአንድ ሰው መታሰር ወይም መሞት ሚሊዮኖችን መተካት እንጂ መሞት አይደለም:: ዛሬ ስንት እስክንድሮች ተፈጥረዋል? ዛሬ ስንት ተመስገን ደሳለኞች ተፈጥረዋል? ለዚህም ነው እኮ አሳሪዎች ማንን ማሰር እንዳለባቸው የሚጠነቀቁት:: የሰው ጥናካሬው የሚለካው በአላማው ነው:: አላማ የሌለው ሰው ፍርክርክ ነው:: መንገዱም አጭር ነው:: አላማውም ከሆዱ ወይም ከቁሳቁስ ያለፈ ካልሆነ አስጊ አይደለም::
          እናም በፈረንጅ ሃገር የምንኖር ሃበሾች በእውነቱ እራሳችንን ወይም አጋሮቻችንን መመርመር አለብን:: አንድ ሰው የመኖረያ ፈቃድ ለማግኘት አስቦ ሰልፍ ሲጠራን ተግበስብሰን መሄድን ማቆም አለብን:: እውነተኛ የሀገር እና የህዝብ ፍቅር ካለን ግን አካሄዳችንን ማስተካከል አለብን:: እውን ሃገሬን እወዳለሁ? ማለት አለብን:: ለምንድን ነው ሃገሬን የምወደው ብለን ራሳችንን መጠየቅ አለብን:: የተማርነው ደግሞ ሃገራችንን ከወደድን ገንዘብን እና ምቾትን ትተን ወደ ሃገራችን ተመልሰን ሃገራችንን ማግልገል አለብን:: "አሳሪ ወይም ገዳይ አለ" ብለን ከፈራን ግን ሃገራችንን ሳይሆን እራሳችንን ነውና የምንወደው ዝም እንበል:: ፓለቲካው ላይ ያሉትን ሰዎች ስናይ የተማረ ባለስልጣን በስንት መከራ ነው የምናገኘው:: ለምን ሲባል ደግሞ የተማረው ሆዳም እና ምቾት ፈላጊ ስለሆነ ነው:: እውን ሃገራችንን የምንወድ ከሆነ የራሳችንን አካሄድ ማሰብ አለብን:: ለራሳችን የግል ምቾት ተቆርቋሪ ሆነን ሳለ ለሃገር አሳቢ መስለን እኛ የማንደፍረውን ወይም የሸሸነውን ነገር ሌላው እንዲያደርገው መምከርና የሃገሪቱን የወደፊት እጣ ፈንታ ባለህበት እርገጥ እንዲል ማድረግ የለብንም:: ሃገሩን የሚወድ የራሱን ምቾት ወዲያ ጥሎ በፈለገው አካሄድ ለአላማው መቆም አለበት:: መሸሽ ወይም በውጭ ሆኖ ሰልፍ መውጣት ሃገርን መውደድ አይደለም:: እናስብ:: ሃገራችን የተማሩ ልጆቿን ጣልቃ ገብነት ትፈልጋለች:: ያልተማሩ እና ለሆዳቸው ያደሩ እየመሯት ታድጋለች ማለት የህልም እንጀራ ነው:: ቢሆንማ ኖሮ ባለፉት 40 አመታት ብቻ የብልጽግና ማማ ላይ በወጣን ነበር:: መስሪያ ቤቶቻችን በተማሩ ሰዎች መሞላት አለባቸው:: ይህንን ማድረግ የሚቻለው ደግሞ የተማረው የሰው ሃይል አላማ ሲኖረውና በሆድ ማሰብን ትቶ በጭንቅላቱ ማሰብ ሲጀምር ነው:: መሸሽ ወይም ሃገር ጥሎ መኮብለል መፍትሄ አያመጣም:: ባለንበት ሆነን የምንፈልገውን ለውጥ ማምጣት እንችላለን:: ጋዜጠኛ "ዋሽ" ሲባል "አልዋሽም" ብሉ መተባበር እንጂ መሸሽ ውሸቱን አያቆመውም:: ፓሊስ "ግደል" ሲባል "አልገድልም" ብሎ መተባበር እንጅ ስልጣንን ማስረከብ መፍትሄ አይደለም:: ባለስልጣንም "ዋሽ" ወይም "አስገድል" ወይም "ሃገር ሽጥ" ሲባል መሸሽ ወይም "ስላጣናችሁን አልፈልግም" ማለት መፍትሄ አይሆንም:: ተቃዋሚዎችም "የውሽት ምርጫ ነው" እያሉ እያማረሩ እዛው ምርጫ ውስጥ መሳተፍና መጨመላለቅ ሳይሆን "አንሳተፍም" ማለት አለባቸው:: የተማርነውም እስኪ ከትንሿ ሃላፊነታችን እንጀምር:: እስኪ የሙያ ሃላፊነታችንን ምን ያህል እንደተወጣን እንፈትሸው:: እስኪ ወደፊት ትምህርቴን ስጨርስ ምን ማድረግ ነው ያሰብኩት እንበል:: ከዛም የፍተሻውን ውጤት ከሃገርና ከህዝብ ፍቅር አንጻር እንመዝነው:: ጎበዝ በምቾትና በሆድ ማሰብን ብናቆምስ?
                                                          ትሮምሶ, ኖርዌይ::

No comments:

Post a Comment