Sunday 5 May 2013

መፅሃፍ አሳታሚዎቻችን

ይህ ፅሁፍ በፌስቡክ ላይ በ ItIs Mee ·Saturday, 22 December 2012  የተፃፈ ነው

እስኪ ዛሬ ደግሞ እዚህም እዚያም የምናያቸዉን መጣጥፎች እንዲሁም መፅሃፍ አሳታሚዎቻችንን እንውረድባቸው::
ታዲያ የሃበሻ ልማድ ሆኖብን ስንተች ወይም አስተያየት ሲሰጠን በክፉ ጎኑ ነው የምናየው እና አስተያየት እንዲሰጣችሁ የማትፈልጉ "ፀሃፍት" ካላችሁ እዚችው ጋ እንሰነባበት:: ከቀሪዎቻችሁ ጋር ትንሽ እንባባል::

ዛሬ ዛሬ በርካታ መጽሃፍት ሲመረቁ ወይም ሳይመረቁ ለገበያ ሲበተኑ ማየት ፋሽን እስኪመስለን ድረስ እያስተዋልን ነው:: ሂደቱ እና መነሳሳቱ እጅጉን ይበል ያሰኛል:: አንባቢን መጨመር እና መኮርኮር ይገባል ብዬ አምናለሁ:: ማንበብ ሙሉ ሰው ያደርጋልና እናንብብ:: ሆኖም ግን ምን እናንብብ? የሚለው ጥያቄ ለንባብ ልምዳችን መዳበር ወሳኝ ሁነት ነው:: አንዳንዶች እንደሚሉትም "አንባቢው መርጦ ያንብብ" በሚለው አላምንም:: አልስማማም:: ለንባብ ባህል መዳበር የፀሃፍቱ ሚናም ወሳኝ ቦታ አለው:: ዛሬ ላይ ሆነን ድሮ ያነበብናቸውን መፅሃፍት እያስታወስን "ዛሬም ማንበብ አለብኝ ያኔ ያነበብኩት ለዛሬ ህይወቴ ትልቅ አስተዋፅኦ አድርጎልኛል" የምንል የእኛ ማንበብ ብቻ ሳይሆን የፀሃፊው አቀራረብ በውስጣችን ያሳደረው በመኖሩ ነው:: በዚያው ልክ ደግሞ ዛሬ ላይ ሆነን "እሱን መፅሃፍ ያነበብኩብትን ጊዜ መመለስ ብችል" ብለን የምንቆጭበትም አለ:: የዚያ ተጠያቂው ደግሞ በስመ ፀሃፊነት ወረቀት ጠርዞ የሸጠልን አፍላ ፀሃፊ ነው:: በኔ እምነት የተሞነጫጨረ ሁሉ አይታተምም:: ቢሆን ኖሮ የሁሉም ሰው ቤት በወረቀት በተሞላ ነበር::

ዛሬስ? ዛሬም የበሰሉ ፀሃፍት እንዳሉት ሁሉ አፍላ ወይም የተርገበገቡ ፀሃፍት ነን ባዮችም ጊዜያችንን እንዳያጠፉት መጠንቀቁ ደግ ይመስለኛል:: መፅሃፍትን ማሳተሙ አለው ብለን የምናስበዉን ዋጋ ያህል አንባቢን በመቀነስም የራሱ ድርሻ እንዳለው መርሳት የለብንም:: ፀሃፍቶቻችን ሲፅፉ ቀድመው ቢያነቡ፣ ቀድመው ቢበስሉ እኛንም ያበስሉን ነበር:: ሆኖም ግን እከሌ/እከሊት አሳተመ/ች በሚል ፈሊጥ ብቻ የወረቀት ጥርቅም ለሽያጭ የሚያቀርቡልን ሰዎች እጅግ ሊያሳስቡን ይገባል:: አንባቢ ይምረጥ የሚለው የሚሰራው የንባብ ልምዱ ለዳበረ ሰው እንጅ አዲስ አንባቢን አይመለከተውም:: አዲስ አንባቢ የመምረጥ ልምዱን ከማዳበሩ በፊት በአፍለኛ ፀሃፊዎች የተጻፉ መፅሃፍት ሞራሉን እንዳይገሉት መጠንቀቅ ከፀሃፍቶቻችን ይጠበቃል::

ወሬዬን አጠር ለማድረግ እባካችሁ "ፀሃፊ" ብላችሁ ራሳችሁን የሾማችሁ ወገኖች የምትጽፉትን ከማሳተማችሁና ለገበያ ከማቅረባችሁ በፊት ብሰሉልን:: እደጉልን:: አደብ ግዙልን:: የረጋ ወተት ቅቤ ይወጣዋልን ለፅሁፋችሁ ማድመቂያ ብቻ አታድርጉት:: ዛሬ ላይ ሆናችሁ በጅብ ችኩል ያሳተማችሁት መፅሃፍ ነገ ስትበስሉ የምታቀርቡትን መፅሃፍ ምች ያስመታባችኋል:: ዛሬ ላይ ሆናችሁ የምታሳትሙት አፍለኛ መፅሃፍ የነገውን በሳል መፅሃፍ እንዳንመለከተው ያደርገናል:: የንባብ ባህል ማዳበር ጅምራችንንም ይገድለዋል:: ከራሳችሁ ዝና በፊች እኛን አንባቢዎችን አስቡን:: እኛን እንደምትሉት እስኪ እናንተም መጀመሪያ አንብቡ:: ያልተፃፈበት አጀንዳ ምን እንደሆነ መርምሩ:: የሌሎችን ሃሳብ እየደጋገማችሁ አትምጡ:: እናንብብ.....> እናዳምጥ....>እንዳብር....>እንጀራ የሚጥመው ሊጡ ሲቦካ ነው:: ቅቤው ነው ጭንቅላታችንን የሚያርስልን::

No comments:

Post a Comment