Wednesday, 22 May 2013

እንዲህ ብናስብስ?

 

የቤተሰባቸውን የእርሻ መሬት ወርሰው በጋራ የሚሰሩ ሁለት ወንድማማቾች ነበሩ፡፡ አንድኛው ትዳር መስርቶ ትልቅ ቤተሰብ ሲኖረው ሁለተኛው ግን ብቻውን ነበር የሚኖረው፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን ወንድማማቾቹ ከቤተሰባቸው የወረሱትን ሀብትና ራሹጽን ንብረት በመከፋፈል በየግላቸው ለመስራት ይስማማሉ፡፡ ያለውንም ሀብት እኩል ተከፋፍለው የየግላቸው ኑሮ ይጀምራሉ፡፡ ወድያውኑ ግን ብቻውን የሚኖረው ወንድሙ ከራሱ ጋር መነጋገር ይጀምራል “ያለውን ሀብትና ትርፍ እኩል መከፋፈላችን አግባብ አልነበረም፡፡ እኔ ብቻየን ነው የምኖረው የሚያስፈልገኝ ነገር በጣም ትንሽ ነው፡፡ እርሱ ግን ብዙ የቤተሰብ ሀላፊነት አለበት” በማለት ያስባል፡፡ እናም በጎተራው ካለው እህል አንድ ጆንያ የሚሆነውን ሁል ግዜ ማታ ማታ እየተደበቀ ወንድሙ ጎተራ ውስጥ ማስገባት ይጀምራል፡፡
በተመሳሳይ ግዜ ሚስትና ልጆች ያሉት ወንድምም በተመሳሳይ ሁኔታ ያስባል “ይህንን ሀብት እኩል መካፈል አልነበረብንም፡፡ እኔኮ ትዳር አለኝ፡፡ ሚስቴና ልጆቼ ሁል ግዜ ከጎኔ በመሆናቸው ወደፊት በደንብ ይንከባከቡኛል፡፡ ወንድሜ ግን ብቸኛ ነው፡፡ ወደፊት አጠገቡ ሆኖ የሚንከባከበው እንኳ የለውም” እያለ ያስባል፡፡ እርሱም እንደዚያኘው ወንድም በጎተራ ካለው እህል አንድ ጆንያ የሚሆነውን ሁል ግዜ ማታ ማታ እየተደበቀ ወንድሙ ጎተራ ውስጥ ማስገባት ይጀምራል፡፡ ወንድማማቾቹ በዚህ ሁኔታ ብዙ ግዜ ኖሩ፡፡ ከብዙ ግዜ ብኋላ ግን ሁለቱንም አንድ ነገር ያስገርማቸው ጀመር፡፡ በጎተራቸው ውስጥ ያለው እህል መጠን እየቀነሰ አለመሄዱ ግራ ያጋባቸዋል፡፡ ሁለቱም የገጠማቸውን ያልተለመደ ነገር ለመመርመር በየግላቸው እየጣሩ ሳለ ከእለታት አንድ ቀን ሌሊት ላይ የተለመደውን ተግባራቸውን ለመፈጸም እህል የተሞላበት ከረጢት እንደተሸከሙ በድንገት ተገናኙ፡፡ ምንም አይነት ቃላት ሳይለዋወጡ ሸክማቸውን መሬት ላይ በመጣል በፍቅር ተቃቅፈው አለቀሱ፡፡ ሲያደርጉ የነበረውንም ሁሉ ተነጋገሩ::


መልእክት:- በዛሬ ግዜስ ይህንን አይነት እውነተኛ ፍቅርና መተሳሰብ ያለው ቤተሰብ ይኖር ይሆን? ሰው ነንና ሁሌም ግለኝነት ያጠቃናል:: ሆኖም ግን አንዳንድ ግዜ እንዲህ አይነት ታሪክ ያላቸው ቤተሰቦች ወይም ጓደኞች ሲያጋጥሙን በአይናችን እምባ መሙላቱ አይቀርም:: "ለምን እንዲህ አልሆንኩም?" እያልንም ራሳችንን እንወቅስ ይሆናል:: እንዲህ ያለውን መተሳሰብ በቤታችንና በጓደኝነታችን ውስጥ አምላክ ይጨምርልን::

No comments:

Post a Comment