Sunday, 5 May 2013

የአርባ ጉጉን ጭፍጨፋ ማን መራው?

አርባ ጉጉ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ጥቁር ጠባሳ ካላቸው ውስጥ ይመደባል:: በወቅቱም ከባድ የሚባል ዘር ማጥፋት የተደረገበት ቦታ ነው:: የተካሄደውን የዘር ማጥፋት የሚያውቁና እውነታውን የሚናገሩ ግን እምብዛም አላገኘሁም ወይም አላጠገቡኝም:: በቅርቡም በኢሳት ላይ እየቀረበ ያለ አንድ ከፍተኛ የመንግስት ሃላፊ የነበረ ሻለቃ መሳፍንት ጥጋቡ የተባለ ሰው ገረፍ ገረፍ በማድረግ አልፎታል:: ከዚህ በፊትም እናውቃለን የሚሉ ነገር ግን የሚያውቁት የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ብቻ ያስተላለፈውን ለራሳቸው እንዲመች አድርገው ሲያወሩ አዳምጬም አውቃለሁ:: ሌሎች ተንታኝ ነን የሚሉም ያሉትን ሰምተናል:: ነገር ግን ሁሉም የሚሉት ውሃ አይቋጥርም:: ምክንያቱ ለግዜው ግልጽ ባይሆንም የማውቀውን ማካፈሉ በጥቂቱ እውነታውን መረዳት ያስችላል ብዬ አስባለሁ::
እውነታው በአጭሩ:-

አርባ ጉጉ የት ይገኛል?
በቀድሞው አርሲ ክፍለ ሃገር ስር የነበረ አንድ አውራጃ ነው ወይም በአሁኑ ወቅት በአርሲ ዞን ስር በመርቲ እና ጀጁ ወረዳዎች ተጠቃለው ያሉትን ክፍሎች ይወክላል:: በቀድሞው የአውራጃው ዋና ከተማ አቦምሳ ወይም ትንሳኤ ብርሃን ስትባል በአሁኑ ግን ይህች ከተማ ለመርቲ ወረዳ ብቻ ስታገለግል ለጀጁ ወረዳ ደግሞ አርቦዬ ወይም ፈለገ ህይወት የምትባል ከተማ እንደ ዋና ከተማነት ያገለግላሉ::

የአርባ ጉጉ ዘር ማጥፋት የት ና መቼ ተካሄደ?
በ1984 ዓ.ም. ሲሆን ጭፍጨፋው በዋናነት የተካሄደው በጠቅላላው ለማስቀመጥ ያህል ከባሌ ድንበር (ከዋቤ) ጀምሮ በደጋማው ክፍል ያሉትን የአኖሌን አካባቢ ይዞ ወደ ጮሌ መስመር ይዘልቅና እስከ መቻራ ድረስ አካሎ ወደ ጉና; አንጋዳ ወይም ተፈሪ ብርሃን የምትባል ትንሽ ከተማን ይዞ አቦምሳ ይዘልቃል:: በመቀጠልም በመሃል ያሉትን የገጠር ክፍሎች ይዞ ወደ አርቦዬ ይዘልቅና ወደ ደጋው ይመለሳል:: እዚህ ላይ በዋናነት የሚነሳው እና ከፍተኛ ውጊያ ሲካሄድ የነበረው አሼ(አብዛኛው ሰው ከሸዋ ምንጃር የመጡ ሰዎች በብዛት የሚኖሩበት) እንዲሁም ደጋው ክፍል ላይ የነበሩት አማሪኛ ተናጋሪዎች የሰፈሩባቸው ቦታዎች ክፉኛ የተጠቁት ነበር::

ጥቃቱ ምን ይመስል ነበር?
በወቅቱ በተካሄደ ብጥብጥ የተጎዱት አብዛኞቹ ማለት በሚቻልበት መልኩ የአማሪኛ ተናጋሪ የሆኑ ነበሩ:: ሆኖም ግን ከነዚህም በተጨማሪ ኦሮሚኛ ተናጋሪዎችም ክፉኛ ተጎድተዋል:: በወቅቱ ሲደረግ የነበረውም ድርጊት አብዛኛው ማለት በሚቻል መልኩ ሃይማኖታዊ ትንኮሳ ያየለበት ነበር:: ለምሳሌ በአርቦዬ ከተማ ሲካሄድ የነበረ (ይህች ከተማ በደርግ ግዜ አማሪኛ ተናጋሪዎች የሚበዙባት ነበረች:: አሁን ተቀይራለች) ድርጊትን ብናይ ቀሳውስትን ሰብስበው ያመጣሉ ገበያ መሃል ላይ ማማ (የእጨት አልጋ) በመስራት እንዲወጡ ያደርጉና "አላሁ አክበር" በል ወይም "ሞትን ምረጥ" በማለት ዙሪያዉን መትረየስ ያጠምዱበታል:: የፈራ ይላል ያልፈራ ግን ገበያ መሃል መስዋእት ይሆን ነበር:: ይህ ድርጊት ታዋቂ የነበሩ አማሪኛ ተናጋሪዎችንም ያካተተ ነበር:: በጮሌና ጉና ወረዳዎችም የማይተናንሰ ስራ ሲሰራ ነበር:: ሆኖም ግን በብዛት ተጎጂ የነበረው ደጋው ክፍል ይኖር የነበረው ነው:: ሰዎችን ከመግደል በተጨማሪም ቤተ ክርስቲያናትንም የማቃጠሉ ስራ እጅጉን የበዛ ነበር:: ከነዚህ ውስጥ ፈረቀሳ የሚባል ቦታን ይዞ ከአርቦዬ መልስ ወደ ላይ ወደ ደጋው ክፍል ያሉት ባብዛኛው እንዲቃጠሉ ተደርጋዋል:: ሆኖም ግን አንዳንድ ኦሮሚኛ ተናጋሪ የእስልምና ተከታዮች መሳሪያ በመያዝ የኛ ነው አትነኩም እያሉ ያተረፉዋቸው ቤተ ክርስቲያናት አሉ:: ለምሳሌ ፈረቀሳ አካባቢ የሚገኝን ጃዊ ስላሴ እንዳያቃጥሉት ከፍተኛ ጥበቃ ሲያደርጉ የነበሩት ሙስሊሞቹ ናቸው (በነገራችን ላይ ጃዊ ማለት አንዱ የአርሲ ኦሮሞ ጎሳ ነው):: በተመሳሳይ ወደ ዲክሲስ መስመር ላይ ያለችንም አሽሚራ ኪዳነ ምህረት ቤተ ክርስቲያንንም አድነዋል:: ሰው ከመግደል እና ቤት ከማቃጠል በተጨማሪ ከብቶችን ወደ ባሌ ማሸሽ; ማረድና ብሉ ማለት (አራጁ ሙስሊም ብቻ ነበር); አማሪኛ ተናጋሪ የሆነና እምብዛም ደስ ያላላቸውን ሰው ሰባራ መርፌ እንኳ ሳይዝ በመሳሪያ ከበው አቦምሳ ወይም አርቦዬ ድረስ ወስደው አሳፍረው ሃገሩን እንዲለቅ ያደርጉ ነበር:: ከዚህም በላይ የሚነገሩ በርካታ ጥቃቶች የነበሩ ቢሆንም ለማሳያ ይበቃሉ::

ጥቃቱን ማን አደረሰው?
የዚህ ጥቁር ታሪክ ጠባሳ ሃላፊነት በየግዜው የተለያየ አካል ሲወስደው ወይም ሲለጠፍበት ነበር:: ለምሳሌ ያህል ተቃዋሚዎች ገዥው መንግስት እንዳደረገው ሲያስረዱ ይስተዋላል:: አብዛኛው ሰውም የሚስማማው በዚህ ነው:: በሌላ ወገን ደግሞ ገዥው መንግስት ጥቃቱን ያደረሰው ኦነግ እንደሆን እየማለ ይነግረናል:: ሆኖም ግን የአጀማመሩ እውነታ ከዚህ የተለየ ነው:: የዚያ ጥቃት አስጀማሪ በወቅቱ ይንቀሳቀስ የነበረው "አሊቲሃድ" የተባለ የሙስሊም አክራሪ ቡድን ነው:: ጅማሮዉም ቅድም እንዳልኩት ከላይ ከደጋው ክፍል አኖሌ አካባቢ የነበሩትን በሃይማኖት አክራሪነቱ አሳምነዋቸው ስለበር በገበያ ቀን እንዲጀምሩት ተደርጎ ቀስ በቀስ ወደ ቆላው እንዲዛመት ተደረገ:: ይህ ሁሉ ሲሆን መንግስት በወቅቱ ለራሱም ያልተረጋጋ ስለነበር ምላሽ የሚሰጥ የበላይ አካል አልነበረም:: ይህንን ተመርኩዞ በአካባቢው (በአውራጃው ከሃረሮች ጋር በመገናኘት) ከፍተኛ ሊባል የሚችል የጦር መሳሪያ ዝውውር እና ሽያጭ ህጋዊ እስኪመስል ድረስ ሲካሄድ ነበረ:: ይህ በመሆኑም ልጅ አዋቂው የጦር መሳሪያ ይዞ እራሱን መጠበቅ ወይም ለማጥቃት ከፍተኛ ዝግጅት ተደረገ:: አሁንም የአገር ሽማግሌዎች መንግስትን ቢጠይቁም ምላሽ አልነበረም:: እናም ከላይ የጠቀስኳቸውን ጥቃቶች በክርስቲያኖች ላይ ተደረጉ:: በ1984 ዓ.ም. መገባደጃ አካባቢ ላይ ግን እልቂቱ እየባሰበት እና ጥቃቱ መዛመት ሲጀምር መንግስት ወታደሮችን ላከ:: እዚህ ላይ ትልቁ የታሪክ መዛባትን ያስከተለው አንዱ ነጥብ ይህ ነው:: እነዛ ወታደሮች እነማን ነበሩ? ወታደሮቹ የሻእቢያ ወታደሮች ነበሩ:: ነገሩን ያበርዳሉ ተብለው የተላኩት ቁጥራቸው አናሳ ግን ነበረ:: ይህም በመሆኑ ቆለኛው ብዙም ሳያስቸግር ዝም ሲል ደገኛውን ግን በቀላሉ ሊገላገሉት አልቻሉም:: እናም አሽሚራ በተባለ ቦታ ላይ ሁለት የአሊቲሃድ አባላት ብቻ በፈረስ ላይ ሆነው ሜዳ ለሜዳ እያባረሩ 30 የሻእቢያ ወታደሮችን ጨፈጨፉ:: በነጋታው በአርቦዬ በኩል አንድ ክፍለጦር እንዲመጣ ሲደረግ አሊቲሃዶቹ ወደ መቻራ ተሰደዱ ሳይያዙም ቀረ:: በዚህ ግዜ አውጡ በሚል ሌላ ተጨማሪ ድብደባና ግድያ ደግሞ በወታደሮቹ ተፈጸመ:: ይህ ከሆነ በሗላ የሻእቢያዉን ጦር ወደ አዲስ አበባ መልሰው የህወሃትን ጦር አመጡ:: ሆኖም በተወሰነ መልኩ ተረጋግቶ ስለነበር ብዙም አልተቸገሩም:: ወዲያው መልሰው የህወሃትን ጦር በብአዴኑ ጦር (ዋለልኝ) እንዲተካ ተደረገ:: ነገር ግን የመንግስት ጦር ወጣ ገባ የማለት አዝማሚያ ስለነበር በሌሊት እየመጡ ከባድ ጉዳት ሲያደርሱ ነበር:: በወቅቱ ከነበሩት የኦህዴድ አመራሮችም በሌሊት ክፉኛ የተደበደቡና የተገደሉም ነበሩ:: ጅብ በቀደደው ውሻ እንዲሉ ሌሊት እየመጡ ባንክ የሚዘርፉ; ሃብታሞችን የሚዘርፉ ነበሩ:: ዘራፊው ማነው ሲባል በወቅቱ ኦነጎች ናቸው ይባል ነበር:: (እዚህ ላይ "ኦነግ" ምንድን ነው ብለው የገጠር ሰዎች ሲጠይቁ "ኦሮሞ ነጻ አውጪ" ማለት ነው ሲባሉ "ኢኑ ነጣ ሂንባኔ ኑ ነጣ ባሳ? " ሲሉም ነበር:: ነገር ግን ያንን ጭፍጨፋ ኦነግ አላደረገዉም:: መንግስትም አላደረገዉም:: የመንግስት ትልቁ ጥፋት በወቅቱ መልስ አለመስጠቱ እንዲሁም መጨረሻ ላይ የተላከው የዋለልኝ ክፍለጦር ክፍልን እንደመላክ መጀመሪያ የሻእቢያዉን ጦር ከዛ የህወሃትን ጦር መላካቸው ነገሩ ቶሎ እንዳይቀዘቅዝ አድርጓል:: በኔ ግለሰባዊ እይታ ግን የአርባጉጉ ዋነኛ ተጠያቂ አሊቲሃድ ነው:: የሆነ ሆኖ ነገሩም ቀስ በቀስ ተረጋጋ:: ጭፍጨፋዉን ሲያካሂዱ የነበሩትም የተወሰኑት ተያዙ የተወሰኑትም ጠፉ ተባለ:: ይህንን አስከትሎ ግን ከአማሪኛም ከኦሮሚኛም ተናጋሪዎች የአገር ሽማግሌዎች በየቦታው በመሰባሰብ ህዝብ ከህዝብ ጋር እንዲታረቅ በማድረግ ነገሩ እንዲቀዘቅዝ አድርገዋል:: በዚያን ወቅት የነበረዉን ጭፍጨፋ ሲመሩ የነበሩ ቀንደኛ ሰዎች ተይዘው ታስረው ፍርዳቸውን ጨርሰው አሁን በነጻ እየኖሩ ይገኛሉ:: (በነገራችን ላይ በአርሲ ኦሮሞ ባህል መሰረት የተጣሉ ሰዎችን የወተት ጮጮ ወይም አስታርቀው ሲያበቁ ከብት አርደው በደሙ ላይ እንዲራመዱ ያደርጋሉ:: ጸበኞችም ከዚያ በሗላ ወዳጅ ይሆናሉ::)

የኔ ጥያቄዎች?
1) የአርባጉጉ ነገር ሲነሳ ለምን የአሊቲሃድ ነገር እንዳይነሳ ይደረጋል? ወይም ለምን ይታለፋል?
2) መንግስት በቂ የሆነ መረጃ እንዳለው አያጠራጥርም:: ነገር ግን ለምን ኦነግ ላይ እንዲለጠፍ ተደረግ? እውነታውን ፍርጥርጥ አርጎ ማውጣቱ ተመሳሳይ ጥፋት እንዳይከሰት ያደርጋል እንጂ አይጎዳም::
3) ተቃዋሚዎች ታሪክን እንደታሪክነቱ እንዲቀመጥ ለምን አያደርጉም? ለምን ለፓለቲካ ፍጆታ ብቻ እንዲዉል ያደርጋሉ? በተወሰነም ቢሆን የሚያዉቁ ይኖራሉ ብዬ አምናለሁ::
4) የታሪክ መዝጋቢዎችስ ለምን በህይወት ካሉት የሃገር ሽማግሌዎች እውነተኛውን ታሪክ አጣርተው ለምን አይጽፉም?
ታሪክን ለመመዝገብ የግድ የታሪኩ ባለቤት የሆነው ትውልድ መጥፋት አለበት? እሩቅ እንዳይባል እንኳ አቦምሳም አርቦዬም ከአዲስ አበባ አይርቁም::
5) እውነትን የሚፈልጉ ጋዜጠኞችስ ለምን አካባቢው ድረስ ሄደው ነገሩን አያጠኑም? በዚያ ወቅት ተሳታፊና መሪ የነበሩ ነገር ግን ተፈርዶባቸው ፍርዳቸውን ጨርሰው የወጡትን ማግኘትና መጠየቅ እየቻሉ ለምን የግምታዊ ወሬ ይነግሩናል? ETVን አይቶም የጽሁፍ ዜና መስራት የውሸት ተባባሪነት ነው:: የአርባ ጉጉና የበደኖ ጭፍጨፋ እንደሚለያዩም ማስተዋል ደግ ነው ባይ ነኝ::
የማውቀውን አልኩ:: የረሳሁት ካለም ሳስታውስ እጨምራለሁ:: ፍንጩን ይዞ ታሪኩን የሚዘግብ ሳገኝ ደግሞ እኔም ይበልጥ አነብ ይሆናል:: ያ ታሪክ ግን ደግሞ እንዳይመጣ ሁሌም ጸሎቴ ነው::

No comments:

Post a Comment