Friday 7 June 2013

ፕሮፌሰር መስፍን የዘመኑ አፈወርቅ ገብረየሱስ?

  ይህ ምልከታ የእኔ ሳይሆን ከፌስቡክ ወዳጄ የደረሰኝ ነው:: መልካም ንባብ::
""በአፍራሽ አስተሳሰባቸው የሚታወቁት ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ዛሬም የግብጽን ጦር ገና ከሩቁ እንድንገብርለት ጉትጎታ ይዘዋል :: ፕሮፌሰሩ እያረጁ ሲሄዱ የሃገራቸውን ታሪክ የዘነጉት መሰለኝ:: ለነገሩ ዘመን ተሻጋሪ አኩሪ ታሪካችንን ተቀምጠው ሲያከሽፉት ለሚውሉ ሰው የሃገራቸውን ታሪክ ዋጋ ቢያሳጡትና በተንጋደደ እይታ ቢያዩት ምን ይገርማል? ለተቀማጭ ሰማይ ቅርቡ ይባል የለ::

ሰውየው እኮ ሃገራችን በደም አላባ ስትታጠብ በርሃብ አለንጋ ስትገረፍና ህዝቦቿ በአለም አደባባይ ስንዋረድ የኬንያዊውን የመሃመድ አሚንን ያክል ለሃገራችን ያላበረከቱ ግለሰብ ናቸው:: ዜጎች ያለፍርድ ሲረሸኑ ሲዋረዱ ሃገራችን የጨለማ ዘመን አገዛዘን እያማከሩ ሲሰሩ የነበሩ ሰው ስለሃገር ክብርና ስለሃገር እድገት ብዙም ይገዳችዋል ብሎ መጠበቅ ከሰማይ ደመናን እንደመዝገን ይሆናል::ተማሪዎቻቸው እና ከሳቸው በእጅጉ በትምህርት እና በእድሜ የሚያንሱ ወጣቶች ለሃገራቸው እና ለህዝባቸው ነጻነት ሲዋደቁ ክቡርነታቸው ግን ለንደን እና ዋሽንግተን እየተንሸራሸሩ በነበረበት ወቅት በርሃብ እና በጦርነት እየነደደ ስለነበረው ህዝባቸው አንዲትም ቃል እንደተነፈሱ የሚናገር ታሪክ የላቸውም ::

ጀግኖቹ ወጣቶች እና የተገፉ ኢትዮጵያዊያን ደርግን ድል አድርገው ሃገሪቱን ሲቆጣጠሩ ህዝቡ እንዳይቀበላቸው እና የነበረው ስርአት እንዲቀጥል ሢተጉ እንደነበር የሚታወስ ነው:: እናም ፕሮፌሰሩ ለሃገራችው ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ እድገት ከመስራት ይልቅ የመንገድ ላይ እሾህ በመሆን ሂወታቸውን ሙሉ ሲያወሩ ጊዜ ያለፈባቸው ታሪክ የሚሰራን ተቀምጠው በውሃ ቀጠነ ሲነዘንዙ የከረሙ፣ በተንኮል የተመረዘው አእምሯቸው ዛሬም የእድሜ ብዛት ያላስተማራቸው ግለሰብ ናቸው:: እስኪ ይሄንን ሁሉ ያስባለኝን የፕሮፌሰሩ ሃሳብ ባጭሩ ላስቀምጥ፥

የግብጽ ጦር በአለም አስረኛ ነው የጦር ብዛቱ አንድ ሚሊየን ተኩል ያክላል:: በአየር ሃይሉም ቢሆን በአለም አስራ አራተኛ ነው:: የታንክ ብዛቱ በአለም አራተኛ ነው፣ ቅብጥርሴ እያሉ ነገራቸውን ይቀጥላሉ ሃሳባቸውን ሲያጠናክሩም የቀድሞ ታሪክን እያስታከኩ ለጦርነት የሚገፋፉ የስርአቱ ደጋፊወች ጠግበው ነው ሊሉ ይዳዳቸዋል:: እኔ እስከማውቀው ድረስ አሁን በስልጣን ላይ ያለው መንግስት ከእርሳቸው በበለጠ የጦርነትን ምንነት ጠንቅቆ የሚረዳ እና የጦርነትን አስከፊነት እንደ ክቡርነታቸው በቴሌቪዥን ሳይሆን በተግባር የሚረዳ ይመስለኛል:: እናም የሃገራችንን ጥቅም ለማስከበር በሚደረገው ሰላማዊ እና ፍትሃዊ ስራ ከጎን ከመቆም ይልቅ በተንኮላቸው የማይወዱትን አካል ጠልፎ ለመጣል እስከጠቀመ ድረስ የሃገርን ጥቅም ለመሸጥ ጉጉነታቸውን አይቼበታለሁ::

በጣም የሚገርመው ሰውየው የሃገራችንን የፖለቲካ ፓርቲዎች በጥርጣሬ እንዲተያዩ በማድረግ እና የዲሞክራሲ እድገታችን ሳንካ ሆነው እንደቆዩ ልብ ያለው ልብ የሚለው ይመስለኛል:: እናም ግብጽን በተመለከተ የጻፉት የሃገራቸው ታሪክ ጠፍቶባቸዋል ወይም ሰውየው እርጂናው ጸንቶባቸዋል እንጂ እኛ ኢትዮጵያውያን ጣልያንም ሆነ ሃገራችንን ለመውረር የመጣ ሌላ ወራሪ መቼም ቢሆን በወታደራዊ አቅም በልጠን ሳይሆን በአላማ ጽናት እና እውነተኛነት እንዲሁም በጀግንነት እንደመከትነው እንጂ በመሳሪያ እና በሰለጠነ ጦር ልቀን ስለተገኘን ያገኘነው ድል እንደሆነ ታሪክ አይነግረንም:: ለነገሩ እርሳቸው የህዳሴው ግድብ በዘመነ ኢህአዴግ እንዲሰራ እንደማይፈልጉ እርግጥ ነው:: ግን ሳይሞቱ ኢህአዴግ የጀመራቸውን ግዙፍ ፕሮጀችቶችን ተጠናቀው እንዲያዩ እመኛለሁ:: ቋቅ ይበላቸው እንጂ ግድቡ በወርቅ ከሚጻፉ የወጣቶቹ ድሎች ውስጥ ዋነኛው ነው:: እናም ይመኑኝ ክቡር ፕሮፌሰር እንደሚሰጉት ግብጾቹ አያሸንፉንም ከእንግዲህም ደግሞ ወደኋላ አይመልሱንም ::

በመጨረሻም የፕሮፌሰሩ ድርጊት በጣልያን ወረራ ጊዜ የነበሩ ባንዳ ምሁር የጣልያንን ሃያልነት እና ስልጣኔ እንደምክንያት በመውሰድ የኢትዮጵያ ህዝብ የጣሊያንን ወረራ እንዲቀበል ሲወተውቱ የነበሩትን አፈወርቅ ገብረየሱስን አስታወሰኝ:: ስለዚህ ፕሮፌሰሩን የዘመኑ አፈወርቅ እንበላቸው?? ቸር ይግጠመን::" ከወንድም ኣንተነህ

No comments:

Post a Comment