Monday 17 June 2013

የኢትዮጵያ እግርኳስ አስለቃሽ እንከኖች እና እውነታው


 

ከትናንቱ ከልክ ያለፈ ደስታ ዛሬ መለስ ካልኩ በሗላ የፊፋን ድረገፅ ተረጋግቼ አየሁት:: እናም ብዙ ማለት ቢቻልም ለጊዜው ግን የሚሰማኝን ብቻ ከድረገፁ መረጃ ጋር እያገናዘብኩ ልዘባርቅ ወሰንኩ:: መልካም ንባብ::

ምንያህል ተሾመ መቼ መቼ ቢጫ ካርድ አገኘ?
1ኛ)June 03 2012 ኢትዮጵያ ከደቡብ አፍሪካ ጋር ስትጫወት በ78ኛው ደቂቃ ላይ ቢጫ ተሰጠው:: ለምን ተሰጠው ወይም በማን ላይ ፋውል ሰርቶ የሚለውን ለ"ስፓርት ጋዜጠኛ" ተብዬዎቻችን ልተወው:: ለኛ ለተመልካቾች ግን ማመሳከሪያ ይሆን ዘንድ የሚከተለውን መረጃ ከፊፋ ድረገፅ ላይ ኮፒ አድርጊያለሁ በጥሞና ይዩት:: የምንያህል ስም በቀይ ተከቧል::


2ኛ)March 24 2013 ኢትዮጵያ ከቦትስዋና ጋር ስትጫወት በ 72ኛው ደቂቃ ላይ ድጋሚ ቢጫ ተሰጠው:: በድጋሚ ትንተናውን ይቺን ይቺን እንኳ ለማያስተውሉት ጋዜጠኞቻችን ልተዋት:: ሁለተኛ እነሱን ማመን ጉም መዝገን እንደሆነም ተረድቻለሁ በበኩሌ:: ለኛ ለተመልካቾች ግን ቀጣዩን መረጃ ይመልከቱ::


3ኛ) ይህ በዚህ እንዳለ ምንያህል መጫወት የማይገባዉን የኢትዮጵያ እና ቦትስዋና ጨዋታ ላይ በ June 8 2013 ተጫወተ:: ስለዚህ ያንን ጨዋታ በፊፋ ህግ መሰረት ውጤቱ ለቦትስዋና በፎርፌ ይሰጣል:: ከኢትዮጵያ ላይም 3 ነጥብ ይቀነሳል::

አሁንም የምንያህል ተሾመን በዚህ ጨዋታ ላይ መሳተፍ የሚያሳይ የፊፋን ድረገፅ መረጃ ከታች እንመልከት::

4ኛ) ነገርየው በዚህ ሳያበቃ ምንያህል ተሾመ በድጋሚ በትናንቱ June 16 2013 በተካሄደው ጨዋታም ተሳተፈ:: ስለዚህ አሁንም በፊፋ ህግ መሰረት በድጋሚ የኢትዮጵያ ውጤት ተሰርዞ ለደቡብ አፍሪካ ይሰጣል ማለት ነው:: አሁንም በድጋሚ ከኢትዮጵያ ላይ 3 ነጥብ ይቀነሳል:: ስለዚህ በውጤቱ መሰረት ኢትዮጵያ ከአንደኝነት ወደ ሶስተኝነት ዝቅ ትደረጋለች ማለት ነው:: ለዚህ ጨዋታም ማሳያ ይሆን ዘንድ ቀጣዩን መረጃ ከፊፋ ድረገፅ ላይ አምጥቼዋለሁ:: የዚህ ቅጣት አተያይ እንደ ህግ ባለሙያዎቹ የሚታይ ቢሆንም ህጉን ብቻ ለሚያነብ ግን ይህ እውነታው ነው:: የፊፋን ህግ ለማገላበጥ ሞክሬ ሳይቀጣ የታለፈ ተጫዋች ወይም ቡድን በቀጣዩ ምን አይነት ቅጣት እንደሚጠብቀው የሚያወራ ማግኘት አልቻልኩም:: ተያያዥ ህግ እንዳለ የሚያውቅ ካለ ግን አስተያየት በመስጠት ይህንን ትንተና ማስተካከል ይቻላል:: የሚሆነውን ግን ወደፊት የምናየው ይሆናል:: መረጃውን እንየው, ምንያህልም መሳተፉንም እናስተውል:-


እናም ፌዴሬሽናችን ይህንን እንኳ መስራት የማይችሉ ደነዞች ጥርቅም መሆኑን ታዝቤ የትናንቱን ደስታዬን ያህል ዛሬም በሃዘን አነባሁ:: ግን ምን አመጣለሁ? ምንም:: አይ ፌዴሬሽን እቴ...ወደውጪ ለመጓዝ ተፎካከሩ:: ተጠላለፉ:: መንግስት ግን በነዚህ እንዝህላሎች ላይ አፋጣኝ እርምጃ እንዲወስድ መጠየቅ ይገባናል:: ለዚህም የተቻለንን ያህል ተቃውሟችንን ለማሳየት ፊርማ ማሰባሰብ ይገባናል:: በሌላ ወገን ደግሞ ጋዜጠኞቻችንን እናገኛለን:: እናንተ ለነ እንግሊዝ በርቱ እንጂ ለሃገርማ ምን አግብቷችሁ::የእንግሊዝ ቢሆን ከነሱ በላይ ትናገሩ ነበር:: አይሰሟችሁም እንጂ:: እነርሱ መፈጠራችሁን እንኳ አያውቁም እናንተ ግን ሃገራችሁን ትታችሁ ለነሱ የሚያደርጉትን በሬዴዮ ስታወሩ ትውላላችሁ:: ለይስሙላ በሚመስል መልኩ ሰይድ ኪያር በፌስቡኩ ላይ ተናግሬ ነበር አይነት ማምለጫ ለጥፎልናል:: ነገር ግን ይህ አይደለም ጋዜጠኝነት:: አስቀድሞ መናገር ተገቢ ነበር:: ይህንን አይነት የሃገር ወሳኝ ጨዋታን ትንታኔ መስጠት ጉድለቶች እንዳይኖሩ መከላከልና መጠበቅ እየተቻለ ስለሌላ ስለማያገባን ስታነበንቡ የሬዲዮ ሰአት ትፈጃላችሁ:: አይ ጋዜጠኝነት? እባካችሁ ከቻላችሁ እናንተም ወደተለመደውና ወደሰለጠናችሁበት የማስተማር ሙያችሁ ተመለሱ::
 

ወድ አንባቢያኖቼ:- በንዴት ስለፃፍኩት ይቅርታ እጠይቃለሁ::
ታዬ ነኝ
ወደሌላ ድረገፅ ወይም ብሎግ ባትወስዱት እመርጣለሁ:: Share ማድረግ ስለምትችሉ ማለቴ ነው:: ከወሰዳችሁት ግን የዚችን ምስኪን ብሎግ ማስፈንጠሪያም አብራሁ ለጥፉ:: 

http://tayezeethio.blogspot.com/2013/06/blog-post_17.html

1 comment: